02/09/2025
የፌዴራል የመንግሥት ሠራተኞች የስራ ዉል የሚቆረጥበት የህግ አግባብ ⚖⚖⚖⚖⚖⚖⚖⚖⚖⚖⚖⚖⚖⚖⚖⚖⚖⚖⚖⚖⚖⚖⚖⚖⚖⚖⚖
የፌዴራል የመንግሥት ሠራተኞች በየቢሮዉ ከፌደራል መንግስቱ ጋር በሚያደርጉት የስራ ቅጥር ዉል አማካኝነት በሚፈጥሩት የቅጥር ግንኙነተት አማካኝነት የሥራ ውል በሕግ የሚቋቋመ ሲሆን ይህ በህግ የሚቋቋም የስራ ዉል የሚቋረጠውም በሕግ መሠረት ነው። የስራ ዉል ሊቋረጥ የሚችልባቸዉን ሁኔታዎች አስመልክቶ በፌዴራል የመንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1353/2017 ስር የሥራ ውል የሚቋረጥባቸውን ሁኔታዎችን በዝርዝር ተደንግጎ ይገኛል፡፡
በአዋጁ ስር የስራ ዉል የሚቋረጥባቸዉ የህግ አግባቦች ተብሎ ከተዘረዘሩት ዉስጥ በራስ ፈቃድ የሥራ ውልን ማቋረጥ አንደኛዉ ሲሆን ይህም በአዋጁ በአንቀጽ 135 መሰረት ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ በማንኛውም ጊዜ የሁለት ወር ቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ሥራውን በፈቃዱ ሊለቅ የሚችል መሆኑን ይደነግጋል፡፡ መስሪያ ቤቱ ሠራተኛውን በቀላሉ ሊተካው የሚችል ከሆነ የሁለት ወሩን ጊዜ ሳይጠብቅ ስንብቱን ሊፈቅድለት ይችላል። ነገር ግን የመንግሥት ሠራተኛው ለሥራው እጅግ አስፈላጊና በቀላሉ ለመተካት የማይቻል ሆኖ ሲገኝ ወደ ፊት ከሚቀጠርበት መስሪያ ቤት ጋር በመስማማት የመልቀቂያ ጥያቄው ሠራተኛው ካመለከተበት ቀን ጀምሮ ከአራት ወር ለማይበልጥ ጊዜ ሊራዘም እንደሚችል ተደንግጓል። የሁለት ወር የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ አገልግሎቱን ያቋረጠ የመንግሥት ሠራተኛ ግዴታውን ባለመወጣቱ ለሚደርሰው ጉዳት እንደተገቢነቱ በፍትሐብሔር እና በወንጀል ሕግ መሠረት ተጠያቂ ይሆናል፡፡
ሌላኛዉ በአዋጁ መሰረት የስራ ዉል የሚቋረጥበት መንገድ በችሎታና ብቃት ማነስ ምክንያት በአሰሪዉ አነሳሽነት የስራ ዉል ሊቆረጥ የሚችል ስለመሆኑ ተደንጎጎ የሚገኝ ሲሆን የሙከራ ጊዜውን ያጠናቀቀ የመንግሥት ሠራተኛ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወር በሥራ አፈፃፀም ውጤቱ የችሎታ ማነስ ከታየበት ምክርና ተገቢው የአቅም ማጎልበት የሚሰጠው ሆኖ የመንግሥት ሠራተኛ በተመደበበት ሥራ ላይ የሥራ አፈፃፀም ውጤቱ በበጀት ዓመት ለሁለት ጊዜ ያህል ከመካከለኛ ውጤት በታች ካገኘ በአዋጁ አንቀጽ 137 መሰረት በዕቅድ አፈፃፀም የችሎታ ማነስ ምክንያት ከሥራ የሚሰናበት እና የስራ ዉሉ የሚቋረጥ ይሆናል፡፡
በተጨማሪም ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ከተመደበበት ሥራ ጋር በተያያዘ በብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ሂደት በስድስት ወር ለሁለት ጊዜ ያህል ተመዝኖ ከዝቅተኛ ማለፍያ ውጤት በታች
ካገኘ በብቃት ማነስ ምክንያት ከሥራ ይሰናበታል። ነገር ግን የመንግሥት ሠራተኛውን ከሥራ ማሰናበት የሚቻለው እንደ አስፈላጊነቱ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 47 የሥራ አፈፃፀም ምዘና ዓላማ እና አንቀጽ 136 ላይ የጡረታ መብት ተጠብቆ አገልግሎትን ስለማቋረጥ የተደነገገውን በመከተል ይሆናል፡፡
# #የህግ አማካሪ እና ጠበቃ ሊበን አብዲሳ
# #0923279532/ 0911899569